ኢህአዴግ ያወጀዉን የጅምላ ጭፍጨፋ ለመታደግና ነግ – በኔን ለማስቀረት – ስለ ጎንደር ሁሉም ዜጋ ሃላፊነት አለበት !

ኢህአዴግ ያወጀዉን የጅምላ ጭፍጨፋ ለመታደግና ነግ – በኔን ለማስቀረት – ስለ ጎንደር ሁሉም ዜጋ ሃላፊነት አለበት !

ራድዬ ነጋሺ

Aug 31, 201614100534_1098213996881060_8207612736909654797_n

አንዳንድ ወሬዎች እንደሚሰሙት ከሆነ መንግስት ጎንደርን ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ በሚል ባለው የጦር ሃይል ” እምሽክ” ማድረግ እንዳሰበ መዶለቱን ነው የሚያሳብቁት :: ኦሮምያን አዳክምያለሁ የሚል የተሳሳተ ግምት የያዘው ህወሓት መሩ መንግስት ጎንደር ላይ ያለው እሳት እኔን ሳይበላ አይጠረቃም የሚል ግምት በመያዙ ሁሌ በክርናቸው የሚያስቡት ሃይላት ” ጎንደርንና ጎጃምን ካጎልነው ሌላው በራሱ ይሟሟል ” የሚል ሂሳብ እንዳሰሉ እየተነገረ ነዉ::

ይህ የሚሆን ከሆነ ጎንደርንና ጎጃምን ለብቻቸው መተው ከቶዉኑም አይገባም :: ይህ ማለት  የጅምላ ጭፍጨፋን አማራጭ ያደረገዉ መንግስት ህዝቡን ሲፈጀው እንደፊልም ተቀምጦ እንደማየት ሲሆን ይህም ስህተትነቱ የከፋ የሚሆነው ጭፍጨፋው ከተሳካና ህዝብን ያገናኘው የጭቁኖች ድልድይ እንዲፈርስ ክፍተት ከተሰጠ በቀጣይ ሌላዉም የማይቀርለት በመሆኑም ጭምር ነው::

ኦጋዴኑ እየተረሸነ ሬሳው እንደ አሳ ከባህር እየተጎተተ ሲወጣ, መንደሩንም ከነነዋሪዎቹ በጅምላ ሲያነዱት ኢህአዴግን ከመርገም ዉጪ ኢትዮጵያዊው ሌላ ሃይል አልነበረዉም ችግሩም የኦጋዴኖች ሆኖ ተትቷል::

ጋምቤላውን ቤቱን በግሪደር አፍርሰው ከመሬቱ  አፈናቅለው  ከፊሉን ገድለው ሲጥሉት ህዝቡ አይቶ ሲያዝን መልሰው ” ምን ከፋህ አንተኑ ልናለማ ብለን ነው !” እያሉ ሲዘባበቱበት ከዝምታ ዉጭ የእርዳታ እጅ መዘርጋት እምብዛም አልተቻለም ነበር::

አፋሩ አፈር እንደመሰለ የልማት አዉታሮችን ሲጠብቅ – እነሱው ሲለሙበት, ከፋብሪካዎች በሚወጡ መርዞች የመጠጥ ዉሃውን በክለውበት ሲያልቅ , ሰፋሪዎችን አስገብተው ያለዉን ሃብቱን ተከፋፍለው አይኑ እያየ እየከበሩበት ” ሰው አደረግናችሁ ” ሲሉትና በርሃብ ሲፈጁት ብሎም እንዳሻቸው ሲተኩሱበት  “ወይ አፋር ! እንኳን ሰዉ ግመሎቹም የኢትዮጵያን ባንዲራ ጠንቅቀው ያዉቃሉ ” ከማለት ዉጪ ፋይዳ አልተገኘም ነበር ::

ሙስሊሙ “እንደዜጋ ሁሉንም ከሁሉም ጋር ቻልኩት  ሃይማኖታዊ መብቴን ግን አላስነካም :: ባዛ ! ለከት አለፋችሁ  ” ቢልና ፍጹም ሰላም ሆኖ የጨቋኞችን አይጠረቄነት ሲቃወም ” ሰዎቹ የሚሉትን እንዳልሆኑ ለህዝቡና ለአለም ሁሉ በዘዴ አጋልጦ ገበና ቢስ በማድረጉ ሰበብ በየአደባባዩ ሲገደልና ሲወገር ሌላው  ህዝብ ” እህህ ብሎ ” ከመብገንና ከማለፍ በቀር ሌሎች አማራጮችን አልተጠቀመም ::የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን እያነሳ መንግስትን ቢዚ ማድረግ ሳይቻለው ቀርቶ ዱላው ሁሉ ሙስሊሙ ላይ እንዲያርፍ ሆኗል:: ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጠባሳም አሳርፏል::

አዲሳበባና አካባቢዋ ያሉ ነዋሪ ዜጎች ተፈናቅለው አደባባይ ሲጣሉና ” የአገር ያለህ ,የወገን ያለህ ” ሲሉ ሃገርም ወገንም ሳንሆንላቸው በድርጊቱ በማዘንና በማጉረምረም ብዙ ታልፎ ከርሞ ህዝበ ኦሮሞው በቃ! ብሎ ሲነሳና  ብቻዉን ሲሞት አየ ወገኔ በደልህ መች ጠፋን አቅም አነሰን እንጂ ምን እናድርግ ?,ከየት እንጀምረው እያለ ሰዉ ሲንጓለል , ኦሮሞዉ ከዚህ በላይ መሸከም አልችልም ብሎ የሚያደርገዉን ፍልምያ በሃዘንና በሰቀቀን ከመከታተል ዉጭ አማራጭ ጠፍቶ ወልቃይትን መንስኤ አድርጎ የተነሳው  የጎንደሩ ተቃውሞ ፈንድቶ ጉዳዩን ሃገር አቀፍ ደረጃ ለማድረስ ድልድይ አበጀ::

በተለይ የአማራዉንና የኦሮሞዉን ትግል ወደ አንድነት ያመጣው ይህ ሂደት መንግስት ላይ ምን እንደፈጠረ ሁሉም ያየው ጉዳይ ነው:: ኢህአዴግ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ የአማራዉን ትግል ካኮላሸ ወደ ህብረት የተመጣበትንም መንገድ መዝጋቱን ስለሚያምን ወደቀድሞው የጭቆና አገዛዝ ህዝቡን ለመመለስ ተራ በተራ በአሳማሚው መቅጣትን እንደመፍትሄ ከመዉሰድ እንደማይመለስ እሙን ነው::

ስለዚህም ዶ/ር ደብረጺዎንን ብውፌስቡክ ገጻቸው “…እንኳን ለ 30 ሚሊዮን ህዝብ (ለአማራው ማለታቸው ነው) ለአፍሪካም የሚበቃ መከላከያ አለን….” ብለው የጻፉት ጽሁፍም ሆነ ይህንኑ ያተሙበት  የፌስቡክ ገጽ በርጥም የሳቸው ከሆነ (https://www.facebook.com/Dr-Debretsion-Gebre-Michael-5411…/…) የሌላው ወገን ዝምታ ኢህአዴግ ወደጎንደርና ጎጃም ሃይሉን ሰብስቦ ያሻዉን ለማድረግ ያመቸዋልና ሌላው ህዝብ በመላ ሃገሪቱ  ራሱ መንግስት በመግለጫው ያመነዉን ወንጀሉን በመጥቀስ መብቶቹን በመጠየቅና, የአንድ ወገኑ ደም የሱም ደም መሆኑን በማወጅ  መንግስት በሁሉም አቅጣጫ የተነሳበትን ለማብረድ በመላ ሃገሪቱ ሃይሉን እንዲበታትን በማስገደድ  የጎንደርና ጎጃም ወገኑን ህይወት ሊታደግ የሚገባ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ መጤን ያለበት  ይህ መንግስት የወጠነውና በአቶ ሃይለማርያም የታዘዘው የጅምላ ጭፍጨፋ ከተሳካለት ኢህአዴግ ድሉን የሚያውጀው በያንዳንዱ ዜጋ ኪሳራ ላይ ከመሆኑም ባሻገር በቀጣይ መላ ሃገሪቱን በልበ ሙሉነት ጸጥ ረጭ ለማድረግ የእያንዳንዱን ቤት ከመበርገድ ወደኋላ የማይል መሆኑን በማጤን ሁሉም በጋራ ድምጽን በማሰማት የጨቋኞችን ዘመን ማሳጠር ይገባል::

አላህ ሃገራችንን የሰላምና የፍትህ ያድርግልን

አሜን !

Leave a comment